ሉቃስ 7:1—10፣ ቃሉን ሁሉ በሕዝብ ጆሮዎች በጨረሰ ጊዜ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። 2፣ አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባሪያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። 3፣ ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው። 4፣ እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው፡— ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ 5፣ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል፡ ብለው አጽንተው ለመኑት። 6፣ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። አሁንም ወደ ቤቱ በቀረበ ጊዜ የመቶው አለቃ ወዳጆቹን ወደ እርሱ ላከ፤ አለውም፡— ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፤ 7፣ ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። 8፣ እኔ ደግሞ ከሌሎች በታች የምገዛ ሰው ነኝ፥ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፥ አንዱንም፡— ሂድ፡ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፡— ና፡ ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም፡— ይህን አድርግ፡ ብለው ያደርጋል። 9፣ ኢየሱስም ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ፡— እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም፡ አላቸው። 10፣ የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ባሪያውን ባለ ጤና ሆኖ አገኙት።